EthiopiaNews

ምርጫ ቦርድ የምርጫው የመጨረሻ ውጤትን በህግ በተቀመጠለት የ20 ቀነ ገደብ ውስጥ እንደሚያሳውቅ አስታወቀ።

ቦርዱ ድምፅ ከተሰጠበት ከሰኔ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 20 ቀናት ውስጥ አጠቃላይ ውጤቱን የማሳወቅ ሕጋዊ ግዴታውን ተከትሎ በቀሩት 4 ቀናት ውስጥ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል።

ቦርዱ በስካይ ላይት ሆቴል ትላንት በሰጠው መግለጫ ምርጫ ከተካሄደባቸው 1,139 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የ723ቱን ውጤት ማፅደቁን ያስታወቀ ሲሆን በትላንትናው ዕለትም ውጤታቸው የተረጋገጠ 75 ምርጫ ክልሎች ውጤትን ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ ውስጥ 40ው የሕዝብ ተወካዮች እና 35 የክልል ምክር ቤት ውጤቶች መሆናቸውም ተነግሯል።

የገዥው ፓርቲና የተፎካካሪ ፓርቲ ዕጩዎች ውጤት እንደሚከተለው ታውቋል፦

• የገዥው ፓርቲ (ብልፅግና) ዕጩዎች ውጤት፦ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጎማ 2 ምርጫ ክልል ከተመዘገቡ 108,725 መራጮች ውስጥ የ106,028 ዜጎችን ድምፅ አግኝተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አሸንፈዋል።

በተመሳሳይ የወቅቱ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል ከተመዘገቡ 183,350 መራጮች መካከል 168,787 ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸው ተረጋግጧል።

• የተፎካካሪ ፓርቲ ዕጩዎች ውጤት፦ በአማራ ክልል ከተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እንዲሁም የአማራ ዲሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ከፍተኛ ድምፅ ማስመዝገባቸውን ቦርዱ ገልጿል።

በዚህም መሠረት፦

• ከአብን፦ መልካሙ ፀጋዬ፣ ጋሻው መርሻ እንዲሁም የሱፍ ኢብራሂም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አግኝተዋል።

• ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፦ መሐመድ ቡሽራ መቀመጫ ማግኘታቸው ተረጋግጧል።

• ከአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ፦ ገብረ መስቀል አደም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘታቸው የተረጋገጠላቸው ተወዳዳሪ መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

በምርጫው ሂደት ከግል ዕጩዎችና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በድምሩ በ129 ምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታ ቀርቦልኛል ያለው ቦርዱ የቅሬታዎቹ ይዘትም መራጮችን አስገድዶ ማስመረጥ፣ የወኪሎች መከልከልና መባረር፣ በምርጫ ዕለት ቅስቀሳ ማድረግ እና የወረዳ አመራሮች ጣልቃ ገብነት የሚሉ እንደሚገኙበት ጠቅሷል።

ቦርዱ የቀረቡትን ቅሬታዎች በሚከተለው መልኩ መፍታቱን አስታውቋል፦

• ውድቅ የተደረጉ፦ በ75 ምርጫ ክልሎች የቀረቡት ቅሬታዎች ማስረጃ ባለመቅረቡ ውድቅ ሆነዋል።

• የተነሱ፦ በ10 ምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ራሳቸው ቅሬታቸውን አንስተዋል።

• የተወሰነባቸው፦ በሀላባ አንድ ምርጫ ክልል ላይ ዳግም የድምፅ ቆጠራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላልፏል።

ቦርዱ እስካሁን የ86 ምርጫ ክልሎችን ቅሬታ መፍታቱን የገለፀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ውሳኔ ያላገኙ 43 ምርጫ ክልሎች መኖራቸውንና እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚያገኙ ተገልጿል።

ዘገባው የሪፖርተራችን አቤል አበበ ነው።

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv