LatestNews

በትግራይ ቶጎጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተደረገው የአየር ጥቃት እርምጃ በሽብር በተፈረጀው የህወሃት ቡድን ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነበር – መከላከያ ሚኒስቴር::

ባሳለፍነው ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ቶጎጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አደረገው የተባለው የአየር ጥቃት እርምጃ በሽብር በተፈረጀው የህወሃት ቡድን ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንደነበር የመከላከያ ሰራዊት አስታውቋል፡፡የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለሃገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው ይህን ያስታወቁት፡፡በመግለጫውም የመከላከያ ሰራዊቱ ከ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ሃይል ከትግራይ እንዲወጣና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንዲሰፍር፤ አርሶአደሩም ከጦርነት ቀጠና ነፃ በሆነ መልኩ የክረምት እርሻውን እንዲያከናውን በማሰብ ስራዎች መሰራታቸው ተነስቷል፡፡ይሁንና በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሃት ቡድን ይህንን ሁነት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከሰራዊቱ ነፃ የሆኑ መሬቶችን ያዝኩኝ በማለት እንዲሁም በአየር ጥቃቱ ንጹሃን ተገድለዋል በሚል የሀሰት መረጃ ሲያሰራጭ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ የአየር ጥቃቱ 9 ሰአት ላይ የተፈፀመና በአካባቢው ምንም አይነት የገበያ እንቅስቃሴ ያልነበረበት መሆኑን አክለዋል፡፡ዳይሬክተሩ ጨምረውም የትግራይ ህዝብ እየተሰራጨ ካለው የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ራሱን በመቆጠብ ሰላሙን ይጠብቅ ብለዋል፡፡ መረጃውን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ነው ያገኘነው፡፡