News

አዲስ ነገር – በአለም አቀፍ ደረጃ የኩፍኝ በሽታ በ79 በመቶ መጨመሩ

የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያም የኩፍኝ በሽታ ከተከሰተባቸው ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስታወቀ።
በአለም አቀፍ ደረጃ በሽታው እንደአዲስ አገርሽቶ በ79 በመቶ መጨመሩን የገለጸው ድርጅቱ በፈረንጆቹ 2021 በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠቁ ሰዎች ብዛት 9 ሺህ 665 እንደነበረ አስታውሶ በተያዘው ዓመት ጥር እና የካቲት ወር ውስጥ ግን 17 ሺህ 338 ሰዎች መጠቃታቸውን በድረገጹ አስነብቧል፡፡
የኮቪድ ወረርሽኝ ሲጀምር በ43 የዓለማችን ሀገራት ክትባቶች መራዘማቸውንና ይህም ህጻናትን ጨምሮ 203 ሚሊዮን ሰዎች የበሽታ መከላከያ ክትባቶችን እንዳይወስዱ ማድረጉን ጠቁሟል።
ሶማሊያ፣ የመን ፣አፍጋኒስታን፣ ናይጀሪያ እና ኢትዮጵያ ደግሞ በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሀገራት መሆናቸው ገልጿል፡፡
በአገራቱ ግጭቶች ፣ የሰዎች መፈናቀል እና የጤና መሰረተ ልማት በጦርነት መውደማቸው ለበሽታው መከሰት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንና በፈረንጆቹ 2020 20 ሚሊዮን ህጻናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መውሰድ ሲኖርባቸው ባለመውሰዳቸው በሽታው ለማገርሸቱ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።
ሀገራትና ዓለም አቀፍ የክትባት ኩባንያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ሲልም የአለም ጤና ድርጅት አሳስቧል፡፡