News

አዲስ ነገር – ሰራተኞች የኑሮን ጫና መቋቋም እያቃታቸው በመሆኑ መንግስት በቂ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ተጠየቀ።

አሁን ላይ በሀገሪቱ እየተከሰተ ባለው የኑሮ ውድነት የተነሳ ሰራተኞች የኑሮን ጫና መቋቋም እያቃታቸው በመሆኑ መንግስት በቂ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ተጠየቀ።
ይህ የተጠየቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ133ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ ‘’የሰራተኛ መደራጀት ለሰላም ለምርታማነትና ለኑሮ መሻሻል’’ በሚል የሚከበረውን የዓለም የላባደሮች ቀን ወይንም ሜዴይን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌድሬሽን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
በመግለጫው አሰሪዎችን ብቻ ተጠቃሚ ከሚያደርጉ አሰራሮች ተወጥቶ ሰራተኛውም ለፍቶ ካተረፈው ትርፍ ተቋዳሽ ሊሆን የሚችልባቸው ሁኔታዎች ሊመቻች ይገባል የተባለ ሲሆን አሁናዊ የኑሮ ውድነትን ተከትሎም በርካታ ሰራተኞች ከምግብ አቅም እንኳን ማሟላት እየተሳናቸው ስለመሆኑም ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ መንግስት ያለውን ችግር ከግምት በማስገባት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ የሰራተኛ በነጻ የመደራጀት ፣ የስራ ዋስትናና የዝቅተኛ ደሞዝ ወለል ትኩረት እንዲደረግበት ጥሪ ቀርቧል።