News

አዲስ ነገር – የአዕምሯዊ ንብረቶችን ማስያዣ አድርጎ መበደር የሚቻልበት አሰራር ያስፈልጋል ተብሏል።

እውቀቶች የገቢ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተከትሎ የአዕምሯዊ ንብረቶችን ማስያዣ አድርጎ መበደር የሚቻልበት አሰራር ያስፈልጋል ተብሏል።
ይህ የተባለው የአዕምሯዊ ንብረት ቀን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እንዲሁም በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣንና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዮኒቨርሲቲ በተከበረበት ስነስርአት ላይ ሲሆን በኢትዮጵያ እውቀትን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባት በአዕምሮ ውጤቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡
የፋይናንስ ተቋማትም ይህን ከግምት በማስገባት የወጣቶችን ፈጠራ ማገዝ ይኖርባቸዋል በተባለበት በዚህ መድረክ ባንኮች ለአምሯዊ ንብረት ለማበደር እንዲያመቻቸውና ማስተማመኛም እንዲኖራቸው የሚያግዝ ስርዓት ማለትም የሚቀርበው ሃሳብ በባለሙያዎች የሚተችበትና ትርፋማነቱም የሚረጋገጥበት መንገድ መፍጠር እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ወጣቶች ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የመብት ጥበቃ ያሻቸዋል ያሉት የኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ የሚመለከታቸው አካላት ለመብቶቻቸው ጥበቃና እውቅና በመስጠት ማበረታታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስስበዋል።
በእለቱ ከሚያዝያ 20እስከ ሚያዝያ 22 /2014 ድረስ የሚቆይ የወጣቶች የፈጠራ ስራ አውደ ርእይ የተከፈተ ሲሆን በአውደ ርዕዩ ላይ ከ45 በላይ የፈጠራ ስራዎች ለእይታ በቅተዋል። ዜናው የሪፖርተራችን አቤል አበበ ነው፡፡