News

በአ.አ ዒድ አልፈጥር በዓል ላይ ረብሻ በመፍጠር የተጠረጠሩ 76 ሰዎች ተይዘዋል ተባለ

በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ በነበረው የዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር ላይ ረብሻና ብጥብጥ ፈጥረዋል የተባሉ 76 ግንባር ቀደም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ብጥብጡ በተለምዶ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ መነሳቱ የሚታወስ ሲሆን ግብረሃይሉ ችግሩ ለብጥብጥ መነሻ የማይሆን ሲል በጠቀሰው ምክንያት መነሳቱን ከጠቀሰ በኋላ መንስኤውን እያጣራ እንደሚገኝና ውጤቱንም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
ሁከትና ግርግሩ የስግደት ስነስርዓቱ እንደተጀመረ ነው የተፈጠረው የሚለው የግብረ ሀይሉ መግለጫ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱን ያስታወሰ ሲሆን ነገር ግን በእለቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች ስለታማ ነገሮች፣ የውጭ ሀገር አክራሪዎች አርማና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎች መያዛቸውን አክሏል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች የተጠቀሱትን ቁሳቁሶች ይዘው ጥቃትና በቀል ለመፈፀም ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣታቸውን የሚያመላከት መረጃም አግኝቻለሁ ብሏል፡፡
መግለጫው ጨምሮም ተጠርጣሪዎቹ የፈጠሩትን ሁከትና ግርግር ተጠቅመው ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች የተቀበሉትን ስውር ተልዕኮ ለመፈፀም ጥረት አድርገዋል ያለ ሲሆን በዚህ የተነሳ የጸጥታ አካላት ላይ የአካል ጉዳት እንዲሁም በህዝብና በመንግስት ተቋማት ላይም ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈ አሁን ከተያዙት 76 ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ በቀጣይ ጉዳዩን በማጣራት ሌሎች የድርጊቱ ተሳታፊዎችን በመያዝ ለህግ እንደሚያቀርብም ግብረ ኃይሉ ያስታወቀ ሲሆን በበዓሉ ታዳሚዎች ላይ የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት እንዳልደረሰም አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በይፋዊው የፌደራል ፖሊስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ያገኘነው መግለጫ ይህን ይበል እንጂ ታዲያ በሁከትና ብጥብጡ የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውን ከበዓሉ አስተባባሪዎችና በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲዘዋወሩ ከነበሩ ምስሎች ለመረዳት ችለናል፡፡