News

በግንቦት ወር በአንዳድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊኖር ይችላል ተባለ

አዲስ ነገር – በሚቀጥለው ግንቦት ወር በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ለአዲስ ነገር ገልጿል።

ጊዜው የበልግ ወቅት እንደመሆኑ መጠን በግንቦት ወር ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎች እንደሚጠቁሙት በተለያዩ የአገራችን ስፍራዎች ላይ ጥንካሬያቸውን ይዘው ሊቀጥሉ እንደሚችሉና ከዚህም ጋር ተያይዞ ከቀላል እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በአብዛኛው አካባቢዎች እንደሚኖር ኢንስቲዩቱ አሳውቋል።

ዝናቡ በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ላይ ለሚገኙ ልዩ ልዩ የበልግና የረጅም ጊዜ ሰብሎች እንዲሁም ለቋሚ ተክሎች የዉሃ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያግዛል የተባለ ሲሆን ለአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ዉሃ አቅርቦት መሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረዉም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ከዝናብ የሚገኘውን ውኃ የተለያዩ የዉሃ ማቆያ ዘዴዎችን በመስራት ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ቀጣይ ለሚያጋጥማቸው የውሃ ዕጥረት ለመጠቀም ከመርዳቱ በተጓዳኝ በተለያየ የእድገት ደረጃዎች ላይ ለሚገኙ ሰብሎች አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው የበዛውን ውሃ ከማሳ የማስወገድ ስራ መስራት አስፈላፍጊ መሆኑን የኢንስትዩቱ መረጃ ያመላከታል፡፡ መረጃው የሪፖርተራችን ፍስሃ ደሳለኝ ነው፡፡