News

አዲስ ነገር – ብሪታንያ የጦር መሳሪያን ድጋፍ ለዩክሬን ለማቅረብ ቃል መግባቷ ተሰማ፡፡

ብሪታንያ የሚሳኤል የጦር መሳሪያን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ለዩክሬን ድጋፍ ለማቅረብ ቃል መግባቷ ተሰማ፡፡
በአውሮፓ የሚያደርጉትን ጉብኝት በመቀጠል ብሪታንያ የገቡት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ጋር መክረዋል፡፡
የዩክሬኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለሁለተኛ ግዜ በብሪታንያ ጉብኝት ያደረጉት ዜለንስኪ ብሪታንያ የጦር አውሮፕላኖች ድጋፍ እንድታደርግላት ያቀረቡት ጥያቄ መልስ አላገኘም ተብሏል ።
የሩሲያ ባለስልጣናት ብሪታንያ ለዩክሬን ድጋፍ ለመስጠት የገባችው ቃል እጅጉን አደገኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ጦርነቱ ላይ አንዳች የሚያመጣው ለውጥ የለም ማለታቸውን ኤፒ ዘግቧል።
🇺🇦#ዩክሬን
የመንግስታቱ ድርጅት እህል ከዩክሬን ወደቦች እንዲወጣ የተደረሰው ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደርጋለሁ አለ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ደጋፎች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ ይሄን ያሉት እህል ከዩክሬን ወደቦች እንዲወጣ የተደረሰው ስምምነት ቀነ ገደብ ሊያልፍ 2 ቀናት ብቻ መቅረቱን ተከትሎ ነው፡፡
ግሪፊትስ ለፀጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ ስምምነት ለአዳጊ ሀገራት እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ እንዲራዘም አስፈላጊውን ውይይት ጀምረናል ብለዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ስምምነቱ እንዲራዘም ከተፈለገ ወደ ሌሎች ሀገራት በምልከው የማደበሪያ ግብዓት ላይ የተጣሉ ክልከላዎች ሊነሱልኝ ይገባል ስትል ተቃውሞ ማሰማቷን አናዶሉ ዘግቧል ።

🇨🇩#ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የልማት ማኅበረሰብ (ሳድክ) በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊው ክፍል ወታደሮቻቸውን ሊያሰማሩ ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ ።
የሳድክ ሀገራት ወታደሮች ከምስራቅ አፍሪካ ወታደሮች ጋር ተባብረው በምስራቃዊው ኮንጐ በሚንቀሳቀሰው የኤም 23 ታጣቂ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ነው አር ቲ የዘገበው፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት በምስራቃዊው ኮንጐ በቀጠለው ግጭት 8ዐዐ ሺ ሰዎች መፈናቀላቸው እና 600 ሺ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውም በዚሁ ዘገባ ተጠቅሷል፡፡
🇿🇦#ደቡብ አፍሪካ
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የዩክሬን ጦርነት እንዲቆም መፍትሄ የሚያፈላልግና ከ6 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጣ የሰላም ልዑክ ቡድን ወደ ሩሲያ እና ዩክሬን ሊያቀና መሆኑን አስታወቁ ።
ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ግብፅ ፣ ዛምቢያ ፣ ዩጋንዳ፣ ሴኔጋል እና የኮንጐ ሪፐብሊክ ሀገራት የተካተቱበት የልዑክ ቡድን ለመቀበል ሩሲያ እና ዩክሬን መስማማታቸውን ገልጸው ቡድኑ በቅርቡ ወደ ሀገራቱ ያቀናል ብለዋል ።
ፕሬዚዳንቱ በልዑኩ ዙሪያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር መምከራቸውን እና የሰላም ልዑም ዓላማ የተሳካ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡ የፈረንሳዩ ለሞንዴ ዘግቧል፡፡