ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸው ምርቶች የወጪ ንግድ የ67 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ ወደ ቻይና በምትልካቸው ምርቶች ያገኘችው ገቢ የ67 ነጥብ 9 በመቶ አማካኝ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሀገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ ምርቶቿን ወደ ቻይና ገበያ በመላክ በድምሩ 804 ነጥብ 163 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሏ የተገለጸ ሲሆን ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል ነው የተባለው።
በተለይም በተጠናቀቀው የ2025 በጀት ዓመት የተመዘገበው የ369 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከቀደመው የ2024 ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ251 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡም ተጠቅሷል።
ይህ ዕድገት ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ካቀረበችው አጠቃላይ የ18 ነጥብ 358 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ የቻይናን የገበያ ድርሻ ወደ 4 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉ ሲገለጽ ወደ ቻይና ከሚላኩ ምርቶች መካከልም ቡና እና ሰሊጥ ቀዳሚውን ስፍራ የያዙ ምርቶች መሆናቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው አጠቃላይ የንግድ ልውውጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 29 ነጥብ 12 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ የሁለቱን ሀገራት የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ጥንካሬ የሚያሳይ ነው የተባለ ሲሆን በቀጣይም የቻይናን ሰፊና አማራጭ ገበያ ይበልጥ ለመጠቀም እንዲሁም የሀገሪቱን የኤክስፖርት ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
