የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በወረቀት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሐምሌ 22-24/2018 ዓ/ም እንደሚሰጥ አስታወቀ።
አገልግሎቱ ይሄን ያለው ስለዘንድሮው የ2018 ሀገር አቀፍ ፈተና አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ ነው።
በወረቀት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በትግራይ ክልል፣ ከሐምሌ 22 እስከ ሐምሌ 24/2018 ዓ/ም በመቀሌ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ አገልግሎቱ ገልጿል።
አገልግሎቱ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በአብዛኛው በ6 ዙሮች በበይነ መረብ በተሳካ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልፆ የተወሰኑ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትና የኮምፕዩተር እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች በ4 ዙሮች በወረቀት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ብሏል።
በትግራይ ክልል በበይነ መረብ ለመፈተን ለተመዘገቡ 14,755 ተፈታኞች በስድስቱ ዙር ከሰኔ 23 2018 ዓ/ም ጀምሮ እየተሰጠ ያለ መሆኑን አገልገሎቱ ገልጿል።
በወረቀት ለመፈተን ለተመዘገቡ 15,325 ተፈታኞች ከሐምሌ 22-24/2018 ዓ/ም በመቀሌና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በወረቀት እንዲፈተኑ ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል።
ተፈታኞች ወደመቀሌና አክሱም ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 20/2018 አ.ም በመግባት እና በሐምሌ 21/2018 ዓ/ም ኦሬንቴሽን በመውሰድ መፈተን የሚችሉ መሆኑን አገልግሎቱ ገልጿል። መረጃው ከትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የተገኘ ነው።
