Sports

የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ስድስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው በ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉባቸው የፍጻሜ እና የማጣሪያ ውድድሮች ዛሬ ለሊት በሂውጅን የሚደረጉ ይሆናል።

በዚህም የ3000 ሜትር የሴቶች መሰናክል የፍጻሜ ውድድር ሲከወን የሴቶች የ5,000 ሜትር እና የ800 ሜትር ወንዶች ማጣርያም የሚደረግ ይሆናል። ዛሬ ሌሊት ሊነጋጋ ሲል 11:45 ላይ ጅማሮውን በሚያደርገው የ3,000 ሜትር መሰናል ሴቶች የፍፃሜ ውድድር ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ቅዳሜ የተደረገውን ቅድመ ማጣሪያ ባለፉት መቅደስ አበበ እና ወርቅውሃ ጌታቸው ትወከላለች።

የ18ኛው የአለም ሻምፒዮና የወርቅ እና ብር የሜዳልያ አሸናፊዎቹን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሚያሳትፈው የሴቶች የ5,000 ሜትር ማጣርያ ውድድር ደግሞ ሌሊት 8:25 ሲል ይደረጋል። በመድረኩም የ1500,ሜትር የብር ሜዳልያ ባለቤቷ ጉዳፍ ፀጋይ የ10 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ለተሰንበት ግደይ እንዲሁም ዳዊት ስዩም ለቅዳሜ ለሊቱ የፍጻሜ ውድድር ለማለፍ ውሳኝ የማጣሪያ ፉክክራቸውን ከ42 የአለማችን አትሌቶች ጋር ይከውናሉ።

የ800 ሜትር ወንዶች የቅድመ ማጣርያ ውድድርም ሌሊት 9:20 ሲል ይጀመራል። ኤርሚያስ ግርማ እና ቶሎሳ ቦደና ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለው በቅድመ ማጣሪያው ይወዳዳራሉ። አትሌቶቹ በዚህ ማጣሪያ ድል ከቀናቸው ሀሙስ ለሊት ለሚደረገው የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ማለፍ የሚችሉ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡ ፈይሰል ዛኪር