LatestPolitics

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 11ኛ አዲስ ክፍለ ከተማ እንዲመሠረት የሚደነግገውን አዋጅ አፀደቀ

አዲሱ ክፍለ ከተማ ‹‹ለሚ ኩራ›› የሚል ሥያሜ ተሰጥቶታል

የአዲስ አበባ ከከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 11ኛ አዲስ ክፍለ ከተማ የሚመሠርተውንና በክፍላተ ከተማ ሥር ያሉ ወረዳዎችን እንደገና የሚያዋቅረውን አዋጅ አፀደቀ፡፡

ሁለተኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስምንተኛ የሥራ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ሲደረግ፣ በከተማ አስተዳደሩ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከየካና ከቦሌ ክፍላተ ከተማ አሥር ወረዳዎችን አቅፎ ‹‹ለሚ ኩራ›› የተባለ አዲስ 11ኛ ክፍለ ከተማ እንዲቋቋም የሚያደርግ ሲሆን፣ የወረዳዎች ሽግሽግና የአከላለል ማሻሻያዎችንም ያደርጋል፡፡

ለሚ ኩራ የተባለው አዲሱ ክፍለ ከተማ አሥር ወረዳዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም ወረዳዎች የተመሠረቱት ከየካ ወረዳ 12 ተከፍለውና ከየካ ወረዳ 13 ተጨምሮ፣ ከቦሌ ወረዳ 10 እንዲሁም ወረዳ 11 ተውጣጥተው የተመሠረቱ ወረዳዎችን የሚይዝ ይሆናል፡፡

በዚህም መሠረት የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም፣ አያት፣ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳ እንዲሁም አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች በአዲሱ ክፍለ ከተማ የሚካተቱ ይሆናል፡፡

በተደረጉ የወረዳ ማሸጋሸጎችም በአሥር ክፍለ ከተሞች ሥር የነበሩ 116 ወረዳዎችን ወደ 120 እንዲያድጉ አድርገዋል፡፡