LatestNews

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ6 ወራት የሥራ ክንውን መገምገሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገመገመ፡፡

ግምገማው በከተማው ከተቀመጠው ግብ አንጻር የተቃኙ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የስራ አፈጻጸም አቅርበዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በ632 ቦታዎች ከ1 ሺህ 338 ሄክታር በላይ መሬት በህገወጥ መንገድ መያዙን ጠቅሰው፥ 322 ባለቤት አልባ ቤቶችና ህንፃዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የኮንደሚኒየም ቤቶችን በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የማስጠናት ስራ የተሰራ ሲሆን በጥናቱም 21 ሺህ 695 መረጃ ማቅረብ ያልቻሉ፣ ባዶና ተዘግተው ያሉ፣ በህገወጥ መንገድየተያዙ ቤቶች መለየታቸውን አንስተዋል፡፡

177 ሺህ 730 የቤት ባለቤቶች ዝርዝርና በመስክ በተሰበሰበው መረጃ መካከል የ132 ሺህ 678 ቤቶች የስም ልዩነት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

10 ሺህ 565 ህገወጥ የመንግስት መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው እና 4 ሺህ 76 ህገወጥ የመንግስት ንግድ ቤቶች መገኘታቸውም ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማፅዳት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉ የተጠቀሰ ሲሆን፥ ባለቤት አልባ ህንፃዎችን የከተማ አስተዳደሩ ተረክቦና በግልፅ ጨረታ እንዲሸጥ በማድረግ ገቢው ለልማት እንዲውል ተወስኗልም ብለዋል።

የኮንደሚኒየም ቤቶች የጥናቱን ውጤት መነሻ በማድረግ የማረጋገጥ ስራ በመስራት በዚህ ሂደት አልፈው ነፃ የሆኑ ቤቶችን ለ1997 ተመዝጋቢዎች በዕጣ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡