LatestNews

የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ::

የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ለበዓሉ በሠላም መጠናቀቅ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የዘንድሮው የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከከተማው የተለያዩ አካላት ጋር በጋራ መስራቱንም ጠቅሷል።

በተለይም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት እና ከሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች እንዲሁም ከወጣቶች ጋር ውይይት በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራውን አጠናቆ ወደ ተግባር መግባቱን ነው ያስታወቀው።

ኮሚሽኑ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና ህብረተሰቡን አጋዥ በማድረግ ባከናወነው ተግባር የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን ገልጿል።

በልዩ ልዩ አደረጃጀት የሚገኙ የከተማዋ ወጣቶች በከተራውም ሆነ በበዓለ ጥምቀቱ ዕለት ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ለበዓሉ ሰላማዊነት ህብረተሰቡን በማስተባበር ለሰሩት ስራ ኮሚሽኑ ምስጋና አቅርቧል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እና ሌሎች የፀጥታ አካላት በዓሉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድካማቸውን ተቋቁመው ያለ እረፍት በመስራት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በትጋት በመወጣታቸው እና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማስቻላቸውን ኮሚሽኑ እስታውቋል፡፡

በእነዚህ በዓላት ወቅት የታየው የወጣቱ ሰላም እና ፀጥታን የማረጋገጥ ፍላጎት እና ተነሳሽነት በሌሎች መደበኛ የፀጥታ ማስከበር ስራዎች ላይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ አንዳለ በጃንሜዳ በከተራና በጥምቀት በዓል ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በበአሉ ታዳሚ ዘንድ የነበረውን ግፊያ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም 5 የስርቆትና አንድ የቅሚያ ወንጀል መፈፀማቸውንም ጠቅሷል።

አንድ ግለሰብም አደንዛዥ እፅ ይዞ ሲንቀሳቀስ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኮሚሽኑ መግለጫ አመልክቷል።

በአጠቃላይ ወንጀሉን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን የተሰረቁ ሞባይሎችም በተጠርጣሪዎች እጅ መገኘታቸው ታውቋል።