EthiopiaNews

የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና መጀመሩን በመዲናዋ እየተሰጠ ነው።

የ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በዛሬው ዕለት በመላ ሀገሪቱ እየተሰጠ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የፈተና ማዕከል በመገኘት የፈተናውን ሂደት በይፋ አስጀምረዋል።

ፈተናው በተለያዩ ዙሮች በበይነ መረብ እና በወረቀት እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ የበይነ መረብ ፈተና ዛሬ ተጀምሯል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት የበይነ መረብ የፈተና አሰጣጥ በዚህ ዓመት ወደ 62 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን 563 ሺህ 501 ተማሪዎች በ607 የፈተና ማዕከላት ውስጥ የሚፈተኑ ሲሆን፣ ፈተናው በ6 ዙሮች እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ከዘንድሮ ጠቅላላ ተፈታኞች መካከል 306 ሺህ 456 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ 257 ሺህ 45 ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው።

በወረቀት የሚሰጠው ፈተና ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 1 እስከ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ከሐምሌ 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በኮሌጆች ውስጥ በሚገኙ የፈተና መስጫ ማዕከላት እየተሰጠም ይገኛል።መረጃው ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ ነው።