ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአፍሪካ ፎርዋርድ ጉባኤ ላይ ለመታደም ዛሬ ጠዋት ናይሮቢ ኬንያ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ እና በአፍሪካ አህጉር መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሳደግ ባለመውና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሚገኙበት አፍሪካ ፎርዋርድ ጉባኤ ላይ የሚታደሙ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ-ፈረንሳይ አጋርነት ለፈጠራ እና ለዕድገት በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ለበርካታ ዓመታት ሲተገበር ከቆየውና ፍራንኮ-አፍሪካ ተብሎ ከሚጠራው የተለመደ ግንኙነት ወጥቶ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ያካተተ አዲስ ስትራቴጂ ለመቅረጽ ያለመ መድረክ መሆኑም ተነግሯል፡፡
አፍሪካን የጥሬ ዕቃ ላኪ ከመሆን አውጥቶ ወደ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለማሸጋገር የሚያስችለው የኢነርጂ ሽግግር፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአፍሪካ የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲያሻሽሉ የሚጠይቀው የፋይናንስ ሥርዓት ለውጥ እና የባሕር ላይ ኢኮኖሚ ልማት በውይይቱ ከሚነሱ ዐበይት ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የዓለም ንግድ ድርጅት መሪዎች ለጉባኤው ከተገኙት መካከል እንደሚገኙበትም ነው የተነገረው፡፡
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv
