LatestNews

ጠ/ሚ ዐቢይ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚደረግበትን የጅማ – ጭዳ አስፋልት መንገድ ግንባታን አስጀመሩ

2.4 ቢሊየን ብር ወጪ ይደረግበታል የተባለው የጅማ ጭዳ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬ ዕለት አስጀምረዋል፡፡ 80 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የጅማ ጭዳ አስፋልት መንገድ ግንባታ በቻይናው ቲ ሲ ጁ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እንደሚገነባ የተገለጸ ሲሆን በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው የተነገረው፣። የግንባታ ፕሮጀክቱን የመሰረት ድንጋይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር በመሆን በኮንታ ልዩ ወረዳ ጭዳ ከተማ አስተዳደር አኖረዋል፡፡

መንገዱ የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎችን የሚያስተሳስር ሲሆን የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት እንዲሁም ከጊቤ 3 እና ጊቤ 4 የኮይሻ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ስራ ጋር ተያያዥ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባ-ጅማ-ቦንጋ-ሚዛን መንገድን ከሆሳዕና-ሶዶ-አርባምንጭ መንገድ ጋር የማገናኘት ተጨማሪ ሚና አለው፡፡

ይህም በቀጠናው የሚገኘውን ከፍተኛ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሃብት ለመጠቀም የሚያስችል ነው፡፡