በአዲስ አበባ ከተማ በግንባታ ሥራ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪያቸውን ጎማ ሳያጸዱ እና የጫኑትን ዕቃ ሳይሸፍኑ በማሽከርከር መንገድ በማበላሸታቸው እንደተቀጡ የከተማዋ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ፣ በከተማዋ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል ከመንገድ ግንባታ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ፣ በተለያየ መልኩ መንገዱንና የትራፊክ እንቅስቃሴውን የሚያስተጓጉሉ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን የገለጹት ሃላፊዋ በተለይ የግንባታ ሥራ የሚሠሩ አሽከርካሪዎች የተሽከርካሪያቸውን ጎማ ሳያጸዱና የጫኑትን የተለያዩ ተረፈ ምርቶች ሳይሸፍኑ በመንቀሳቀስ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ይህንን ሕገወጥ ተግባር ለማስቀረት በአንድ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተጀመረው የቁጥጥር ሥራ፣ አሁን ላይ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ ለበርካታ አሽከርካሪዎች ተደጋጋሚ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራቱን በመግለጽ፣ በግዴለሽነት የተሽከርካሪያቸውን ጎማ ሳያጸዱ በከተማዋ የአስፓልት መንገድ ላይ በማሽከርከር መንገዱ እንዲቆሽሽና እንዲበላሽ ያደረጉ አካላት እንዲቀጡ መደረጉን አክለዋል።
በዚህም በርካታ በጀት ተመድቦ የተገነባው የመንገድ መሠረተ ልማት በመበላሸቱ፣ ተጨማሪ ወጪ ወጥቶ እንዲጠገን ተደርጓል ያሉ ሲሆን በከፍተኛ በጀት የተገነባው የመንገድ መሠረተ ልማት በአጠቃቀም ችግር ምክንያት እንዳይበላሽ፣ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
