በ2018 በጀት አመት በመዲናዋ የመብራት ምሠሶ (ፖል) ከገጩ አሽከርካሪዎች የጉዳት ካሳ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ይሄን ያለው በ2018 በጀት አመት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ነው።
ከተቋቋመ ሁለት አመት ያልሞላው የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን የከተማዋን መብራት ለማዘመን እየሰራ እንደሚገኝ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰብስብ ሁሴን (ዶ/ር ) ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በ2018 በጀት አመት በአዲስ አበባ የሚገኙ 41 ሺህ 283 የመብራት ምሰሶዎች መረጃ በጂኦግራፊያዊ መረጃ ስርዓት እንዲደራጁ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህም የከተማዋ የመብራት ምሰሶዎች በዲጂታል የመረጃ ስርዓት ከመያዝ ባለፈ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የመብራት ጥገና ለማከናወን ቁልፍ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ በከተማዋ እየለሙ ያሉ ዘመናዊ የመብራት መሰረተ ልማቶችን ሁሉም ህብረተሰብ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል።መረጃው የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን ነው።
