EthiopiaNews

የቦይንግ ኩባንያ ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የዓለም አቀፉ የስፔስ ሳይንስ መርሃግብር በመከታተል መመረቃቸውን አስታውቋል።

የወደፊቱ የአፍሪካ ስፔስ ተመራማሪዎች ስቴም አካዳሚ በምህፃሩ ፋሴሳ የተባለው ተቋም ከአሜሪካው የቦይንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ባካሄደው 3ኛው ዓመታዊ (ፓዝ ዌይስ ቱ ስፔስ) መርሃ-ግብር 832 ኢትዮጵያንን ጨምሮ 2,626 አፍሪካውያን ተማሪዎችን አስመርቋል።

ቦይንግ ኩባንያ ለአምስት ወራት በተካሄደው በዚህ የስልጠና መርሃ-ግብር ተማሪዎቹ በአስትሮኖቲክስ፣ ሲስተምስ ኢንጂነሪንግ፤ እና በማቴሪያል ሳይንስ
እና በሌሎች የትምህርት ዘርፎች ላይ ስልጠና የወሰዱ መሆኑን ገልጿል።

ተመራቂ ተማሪዎቹ ከደቡብ አፍሪካ 1,313፣ ከኢትዮጵያ 832 ፣ከ​ናይጄሪያ 431 እና ከ​ኬንያ 50 ተማሪዎች የተወጣጡበት መሆኑን ቦይንግ ገልጿል።

ተማሪዎቹ ከአሜሪካው የናሳ ጆንሰን ስፔስ ማእከል ፣ ከፋይናል ፍሮንቲየር ዲዛይን እና ከተለያዩ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ የስፔስ ባለሙያዎች እና የቀድሞ ጠፈርተኞች ጋር በበይነ መረብ የመገናኘት እድል አግኝተዋል።

መርሃ ግብሩ በፈረንጆቹ 2024 ከተጀመረ ወዲህ በአጠቃላይ ወደ 3,500 ለሚጠጉ አፍሪካውያን ተማሪዎች ተደራሽ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።መረጃው ከቦይንግ ኩባንያ የተገኘ ነው።