በከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ስር ከሚገኙ ሆስፒታሎች አንዱ በሆነው በጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል የ26 ዓመቷ እናት አራት ህፃናትን በሰላም ተገላገለች።
የመዲናዋ የጤና ቢሮ ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት እናትየው እና አራቱም ልጆችዋ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ ብሏል።
የህክምና ሂደቱን በበላይነት የሰጡትና የመሩት የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር እሸቱ ታደለ እና ሌሎች የሆስፒታሉ የህክምና ቡድን ቀዶ ሕክምናውን በስኬት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር እሸቱ የ26 አመትዋ እናት አራት ፅንስ መፀነስዋን በሆስፒታላችን ክትትል በምታደርግበት ወቅት በመታወቁ ለእናቲቱ እና ለሚወለዱት ጨቅላዎች ደህንነት ከፍተኛ የሆነ ክትትል እንደሚያስፈልግ ከግምት ውስጥ በማስገባት የወሊድ ቀኗ ከመድረሱ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በዋርድ በማስተኛት ሌት ከቀን ክትትል እንደተደረገላት ገልፀዋል።
ዶ/ር እሸቱ በመውለጃ ቀኗም በጨቅላ ህፃናት ክፍል ለህፃናቱ ማረፍያና አጋዥ ማሽኖች ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውሰዋል።
ከሶስት ዓመት በፊትም በተመሳሳይ አንዲት የ24 ዓመት ወጣት እናት በጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል ገብታ አራት ህፃናትን በሰላም መገላገሏን የጤና ቢሮው መረጃ ያሳያል። መረጃው ከከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ የተገኘ ነው።
