የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ በሚገነባው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ከቀረቡት የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች መካከል የቻይና ኩባንያዎች ቀዳሚዎቹ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በሚገነባው በዚህ ፕሮጀክት አብዛኞቹ የቻይና ኩባንያዎች ወይም ከቻይና ጋር አጋርነት የፈጠሩ ኩባንያዎች መመረጣቸውን መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው ሲኤች-አቪዬሽን ዘግቧል፡፡
የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንን ጨምሮ 10 ያህል የቻይና ኩባንያዎች የአውሮፕላን ማረፊያውን ሥራዎች ለመስራት ለመጨረሻው ውድድር የተመረጡ ሲሆን የአሜሪካ፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ሕንድን ጨምሮ የሌሎች አገራት ኩባንያዎችም በዝርዝሩ ተካተዋል።
አየር መንገዱ የመጨረሻዎቹን ኩባንያዎች የሚመርጥበትን ጊዜ ወደ ቀጣዩ ዓመት ጥር ወር ማራዘሙን የጠቀሰው ዘገባው ይፋ የተደረገው የእጩዎች ዝርዝር የቻይና ኢንጂነሪንግ እና ግንባታ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ላይ ያላቸውን የጎላ ሚና የሚያሳይ ነው ብሏል።
