የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ተገለጸ።
ዶክተር መቅደስ የሊቀመንበርነት ኃላፊነቱን የተረከቡት ከማሊ የጤና እና ማህበራዊ ልማት ሚኒስትር አሳ ባዲያሎ ቱሬ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ጉባኤ የኒጀር የሕዝብ ጤናና ንፅህና ሚኒስትር ዶክተር ጋርባ ሃኪሚና የዚምባብዌ የጤና እና የህፃናት እንክብካቤ ሚኒስትር ዶክተር ዳግላስ ሞምቦሾራ የኮሚቴው ምክትል ሊቀመናብርት ሆነው ተሾመዋል።
በዚሁ የጉባኤ መድረክ ላይ በፈረንጆቹ 2035 በአፍሪካ ዘላቂነት ያለው የጤና ፋይናንስ ማረጋገጥ የሚያስችል ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ የሰው ሃብት እጥረትን በተመሳሳይ ዓመት ለመቅረፍ በባለሙያዎች ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በትላንትናው ዕለት መካሄድ የጀመረው ጉባኤው እስከ መጪው አርብ ነሃሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡
