EthiopiaNews

ግብጽ ጊዜው ያለፈበትንና ዘመኑን የማይመጥን አካሄድ ትታ በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን አዲስ እውነታ መቀበል አለባት ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ገለጹ።

የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት አባይን በተመለከቱ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ቆይታ ማድረጋቸውን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ግብፅ አሁን ያለንበት ዘመን 19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን ሳይሆን 2026 መሆኑን በውል ከተገነዘበች ከኢትዮጵያ ጋር አባይን በተመለከተ ሁለቱንም ወገኖች አሸናፊ የሚያደርግ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ቲቦር ናዥ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን በውሃ ሃብቷ የመልማት መብት ግብጽ ልታከብር እንደሚገባም ገልጸዋል።

የቀጣናው ፖለቲካዊ ገጽታ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን የገለጹት ቲቦር፣ ግብፅ በአሁኑ ሰዓት አዲስ የኃይል ሚዛን መፈጠሩንና ኢትዮጵያም እጅጉን ማደጓን ልትገነዘብ እንደሚገባ አስምረውበታል።