ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይና ተቋማት በዮርዳኖስ የአሜሪካ ጦር ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ለኢራን የሳተላይት ምስል አቀብለዋል የሚለውን አነጋጋሪ ዘገባ ማጣጣላቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ “አሜሪካም ቻይናን ስለምትሰልል ድርጊቱ አዲስ አይደለም” በማለት የስለላ ጉዳዩን እንደ ተራ ነገር ቆጥረውታል ነው የተባለው።
ዎል ስትሪት ጆርናል ይዞት የወጣው ይህ ዘገባ የቤጂንግ መንግሥት በቀጥታ እጁ እንዳለበት የሚገልጽ መረጃም ሆነ ምስሎቹን ለኢራን የሰጡትን የቻይና ተቋማት ስም ይፋ አላደረገም።
ጉዳዩ በቅርቡ ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ይነሳ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ ግልጽ የሆነ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል ተብሏል።
የፕሬዝዳንቱ ንግግር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የከረረ ውጥረት ለማርገብና ከቤጂንግ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስቀጠል ያለመ መሆኑ ተመልክቷል።
