በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር በሁለት ዙር 116 መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ስራ እየሰራ መሆኑን የጠቀሰው ኤምባሲው ዜጎች ህጋዊ የፍልሰት አማራጮችን ብቻ በመከተል ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከአካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት እንዲሁም ህይወት ማጣት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርባል።
በሌላ በኩል በውጪ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወደ ሃገር ውስጥ ለመመለስ ከመስከረም 5 ቀን 2018 አመተ ምህረት ጀምሮ በተሰራ ስራ 102 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ ስለመቻሉ ተነግሯል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ያሳወቀው በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 1ሺህ 861 ኢትዮጵያዊያንን በ10 ቀናት የበረራ ምልልስ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ መቀበሉን ተከትሎ ነው፡፡
በእነዚህ 10 በረራዎች 1ሺህ 313 ወንዶች እንዲሁም 485 ሴቶችና 63 ህፃናት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡
