የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሀገራቸው ለማንኛውም ዓይነት ዛቻ እና ጉልበት እንደማትንበረከክ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በሀገራቸው ላይ ያሰማችውን የማውደም ዛቻ ውድቅ በማድረግ፣ ኢራን በሃይል የማንበርከክ ቋንቋን ፈጽሞ እንደማትቀበል አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፣ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ሰፊ ጊዜ እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ግን አሁንም ክፍት አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የኢራን የደህንነት ኃላፊ ሞህሰን ሬዛኢ፣ አሜሪካ በአየር መንገዳቸው ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በሚተገብሩ ሀገራት አየር ማረፍያዎች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ሊያጋጥም እንደሚችል ዛቻ አዘል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ምንም እንኳን በሁለቱ ሀገራት መካከል ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ የቃላት ጦርነትና ውጥረት ቢኖርም፣ ቴህራን አሁንም ለሰላማዊ ድርድር በሯ ክፍት መሆኑን ትናገራለች።
