የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ፣ በአማራ እንዲሁም በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ የትጥቅ ግጭቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ፣ ልዩነቶች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ፣ ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል መሠረተ- ልማቶች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ ጥሪ አቀረበ፡፡
የሕወሓት ቡድን ያሰማራቸው ታጣቂዎች ከመስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም ከለሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ በአማራና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች ጥቃት መክፈታቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በየብስና በአየር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመቋረጣቸው ምክንያት በመሠረታዊ ቁሳቁሶችና አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ክፍተቶች መፍጠሩንም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ የተቀሰቀሰው ግጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በተለይም የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚ አካላት ስምምነታቸውን እንዲያከብሩ እና በሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎችን እንዲያከብሩም አሳስበዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥረት እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
