የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈው በዛሬው ዕለት ባካሄደው 59ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።
ምክር ቤቱ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መልክ ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱ የብሔራዊ የዳታ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ እና ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተደረሰውን የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ኤስ.ዲ.አር ብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን አፅድቆ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መርቷል።
ምክር ቤቱ በፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብ የተወያየ ሲሆን ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱ በፌዴራል ተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መርቷል፡፡
መረጃው ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የተገኘ ነው።
