EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ፖሊስ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ጌጣጌጦችን የሰረቀች ግለሰብ ከነ አባሪዎቿ በቁጥጥር ስር መዋሏን አስታወቀ።

ኢየሩሳሌም በርገኔና አማኑኤል ማቲዮስ የተባሉ ተጠርጣሪዎች የስርቆት ወንጀሉን የፈፀሙት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ዲቦራ ፋውንዴሽን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው።

ፖሊስ ተጠርጣሪዋ ለ1 ዓመት ከ5 ወር ያህል የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራ የነበረች መሆኑን አስታውሷል።

ተጠርጣሪዋ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ጌጣጌጦችን ሰርቃ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ለሚኖር የወንድ ጓደኛዋ ጋር በአደራ ማስቀመጧን ፖሊስ ገልጿል።

የግል ተበዳይን ጥቆማ መሠረት በማድረግ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ሊያውልም መቻሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የተጠርጣሪዋ ፍቅረኛ የሆነው አማኑኤል ማትዮስ ከ4ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣውን 1 የእጅ የወርቅ ሰዓት በ540ሺ ብር አብዱልአፊዝ ነጂብንም ለተባለ ግለሰብ የሸጠ ሲሆን ፖሊስ ገዢውንም በቁጥጥር ስር አውሏል።

ሦስቱንም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ንብረቶቹን ለባለቤቱ ያስመለሰው ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ በመሰብሰብ ምርመራው በተገቢው መልኩ እንደቀጠለ ገልጿል፡፡

ፖሊስ በክፍሉ ዓቃቤ ህግ በኩል ክስ ለመመሰረት ዝግጅት ላይ ሲሆን ያልተመለሱ ንብረቶችን ለማስመለስም ምርመራ የማስፋት ተግባራት መቀጠሉን ነው ያስታወቀው፡፡

ፖሊስ ህብረተሰቡ የቤት ሰራተኛን ሲቀጥር በቂ ተያዥ መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስቧል።