በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ «ምህረት ይደረግልን» የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ለሚገኙና በሳዑዲ አረቢያ ያሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ምህረት የሚሰጠው በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት እንጂ በኤምባሲው አለመሆኑን አስታውቋል።
እንዲሁም ዜጎቹ መኖሪያ ፍቃዳቸውን ለማስተካከልም ሆነ ወደ ሀገር ለመግባት የሳዑዲ መንግሥት ምህረት እንዲሰጣቸው ኤምባሲው በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን እየተከታተለ መሆኑንና ምህረቱ በሚሰጥበት ወቅትም የዕድሉን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ አሳስቧል።
በተጨማሪም በኮንትራት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄዱ ዜጎች ሕጋዊ ሆነውና መብታቸው ተከብሮ ሥራቸውን እንዲሰሩ እንዲሁም ከሥራ ገበታቸው በመጥፋት ለችግር እንዳይጋለጡ ኤምባሲው ጥሪ አቅርቧል።
ኤምባሲው ዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲን መሠረት በማድረግ፣ በሪያድና በአከባቢዋ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብትና ጥቅም ለማስከበር ፣ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማኅበራት ጋር በመተባበር፣ ለተለያዩ ዜጎቻችን ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።
