ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማርኮ ሩቢዮ ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊና ተግባራዊ አጋርነት ለማሳደግ ሁለቱ አገራቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መኾኑን ጠቅሠዋል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ለምታደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሠጠችውን ማረጋገጫ አደንቃለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለትዮሽ ትብብሩን ለማጠናከር እና በቀጣናዊና ባለብዙ ወገን መድረኮች ቅድሚያ በሚሠጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት መንግሥታቸው ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
