የአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ዲስትሪቢዩሽን ኔትዎርክ ማሻሻያ 4ኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት አፈጻጸም ከ66 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
ፕሮጀክቱ በአገልግሎት ዘመናቸው ያረጁ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን በመልሶ ግንባታና በአቅም ማሳደግ ሥራዎች በመተካት የኔትዎርኩን አቅም ለማሻሻልና የኃይል አቅርቦቱን ጥራትና ተዓማኒነት ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።
በ76 ሚሊዮን ዶላር በጀት የሚከናወነው ፕሮጀክቱ በሁለት ዋና ዋና ሎቶች ተከፍሎ በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫዎች እየተተገበረ ይገኛል የተባለ ሲሆን እስካሁን በፕሮጀክቱ 8 ሺህ 914 የኮንክሪት ምሰሶዎች ተተክለው ወደ አገልግሎት መግባታቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም 104 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 56 መጋቢ መስመሮችን የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ሥራ ውስጥ እስካሁን 22ቱ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸው ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈል ኔትዎርክን በማዘመን፣ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስና ከከተማዋ እያደገ ለመጣው የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
