የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል፣ ከሮክ እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል ተጠርጥሮ ከማላዊ ተይዞ ወደ ሀገር እንዲመጣ ባደረገው አድነዉ ባሻዉ ዉዳሞ ላይ ምርመራ አጣርቶ በማጠናቀቅ ለፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን አስታወቀ።
በቀረበው የክስ መዝገብ ዝርዝር መሠረት ተከሳሹ አድነዉ ባሻዉ ዉዳሞ እና ግብረ አበሩ ታምራት ኤርዳዶ ሞሎሮ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ለማሻገር የተደራጀ የወንጀል ቡድን መስርተው በዋና ወንጀል አድራጊነት በመምራት ተጎጂዎችን በሞያሌ፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በማላዊ፣ በዛምቢያና በሞዛምቢክ በኩል ድንበር የማሻገር የወንጀል ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር በምርመራው እንደተደረሰበት ተገልጿል።
ተከሳሾቹ ሕገ-ወጥ ጉዞውን ለማስፈጸም ከእያንዳንዱ ተጎጂ ከ400 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ከፍተኛ ገንዘብ በጥሬ እና በባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ በማስደረግ የተቀበሉ ሲሆን፤ የተጠየቁትን ገንዘብ በወቅቱ መክፈል ያልቻሉ ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በኃይልና በዛቻ በማስጨነቅ ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ሲያደርጉ መቆየታቸውን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያሳያል።
ከዚህም ባሻገር ተከሳሾቹና ግብረ-አበሮቻቸው ተጎጂዎችን ለሰው ማጓጓዣነት ባልተዘጋጁ አየር በሌላቸውና በጣም በተጨናነቁ ኮንቴነሮች፣ በቦቴ እና ሸራ በለበሱ የኤፍ ኤስ አር መኪኖች ውስጥ በመጫን ለከፍተኛ የሕይወት አደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሲያጓጉዟቸው እንደነበርም በፖሊስ የምርመራ መዝገብ ተጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት በርካታ ተጎጂዎች በዛምቢያ፣ በማላዊና በታንዛኒያ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ የረጅም ጊዜ እስራትና እንግልት ማስተናገዳቸው ተገልጿል።
የፌደራል ዐቃቤ ሕግም ፖሊስ በተከሳሾቹ ላይ ሰፊ ማጣራት አድርጎ ባደራጀው መዝገብ ላይ ተመስርቶ ተጠርጣሪዎች ላይ 35 ክስ በመመስረት አሁን ላይ የወንጀል ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
ዋነኛው ተጠርጣሪ አድነው ባሻው ከማላዊ ተይዞ ያለፈው 2018 አ.ም ወደ ሀገር እንዲመጣ መደረጉ ይታወሳል።
