የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብራቸውን በሚሰሩበት ቦታ ሆነው በኦንላይን በተዘረጋው አሰራር በመጠቀም የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በመላክ ክፍያ የሚፈፅሙበት አሰራር መዘርጋቱን አስታወቀ።
ቢሮው ይሄን ያለው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
የቢሮው የታክስ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሚኪያን ሙሉጌታ ከባለፉት 2 ዓመታት ወዲህ በግብር ከፋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ ፣ አገልግሎቶችን ለማዘመን የሚያስችሉ ሁሉአቀፍ የሪፎርም ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በዚህም 2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የደረጃ «ሀ» ግብር ከፋዮች ወርሃዊ የቫት እና የሰራተኞች ደሞዝ ግብር በአካል ወደ ገቢ ሰብሳቢ ተቋማቶች መምጣት ሳይጠበቅባቸው አሳውቀው ክፍያ የሚፈፅሙበት አሰራር ወደ ተግባር ተሸጋግሯል ብለዋል፡፡
የግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ዳይሬክተር ታዬ ማስረሻ በበኩላቸው በዓመታዊ ግብርም ሆነ በወራዊ ቫትና የደሞዝ ገቢ ግብር ማሳወቅ ላይ የተዘረጉ የኦንላይን አገልግሎቶች የግብር ከፋዮች እንግልትና ምልልስ የሚቀርፍ ፣ ግብር ከፋዮች ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ በመቀነስ ብልሹ አሰራር ለመከላከል በመሆኑ ግብር ከፋዮች ለተሟላ ትግበራ የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ቢሮው የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ያለቅጣት አሳውቀው ክፍያ የሚፈፅሙት ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልፆ የሂሳብ መዝገባቸውን በኦንላይን በመላክ በሚደርሳቸው የክፍያ ማዘዣ የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉ አሳስቧል፡፡
