ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም አሜሪካ ባደረገችው አዲስ የሰላም ግፊት መሠረት፤ ከዘጠኝ ወራት በኋላ በአቡ ዳቢ የፊት ለፊት ውይይት አካሂደዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ውይይቱን ገንቢ ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ በአሜሪካ ተደራዳሪዎች አቀራረብ ላይ የታየው ለውጥ እና የእስረኞች ልውውጥ ጉዳይ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ውይይቱ እጅግ ውጤታማ ነበር ያሉ ሲሆን የሩሲያ ተደራዳሪዎች ግን የሁለተኛው ቀን ስብሰባ ሳይጠናቀቅ ውጤታማነቱን ለመገምገም ጊዜው ገና ነው ማለታቸው ተሰምቷል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በበኩላቸው የዩክሬንን ጦርነት ከማስቆም በፊት የአውሮፓ የደህንነት ስምምነት መቅደም እንዳለበት አቋማቸውን በይፋ አንጸባርቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ አገራት በድርድሩ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየጠየቁ የሚገኙ ሲሆን፤ ዩክሬንም የሰላም ጥረቱን በማስቀጠል በሩሲያ ላይ የሚደረገው ጫና እንዲቀጥል አሳስባለች፡፡
