EthiopiaInternationalNews

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኮፕ 31 የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር መምከራቸውን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን፣‎ ከፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስተብ፣ ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስተር፣ ከኢራቁ ፕሬዚዳንት ኒዛር አሚዲ እና ከባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

ከባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የገለጹት ዐቢይ አሕመድ በተለይም በአቪዬሽን ትብብር እና የኢትዮጵያን የኮፕ 32 ፕሬዝዳንትነት ለመደገፍ በሚደረገው አጋርነት ላይ መክረናል ብለዋል።

‎እንዲሁም ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር በነበረን ቆይታ ኮፕ 31ን ለማስተናገድ ለተደረገው ዝግጅት እና ጉባኤው በድምቀትና በስኬት እንዲጠናቀቅ ቱርክ እያሳየችው ላለው ጥረት አድናቆቴን ገልጫለሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

ይህም ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ፕሬዝዳንትነትን ለመረከብ በምታደርገው ዝግጅት ላይ የሚኖረውን አጋርነት እንዲሁም የጋራ ትኩረት በሚሹ ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመተባበር የሚያስችሉ ዕድሎችን ተመልክተናል ብለዋል።

‎ከፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስተብ ጋር በነበረን ቆይታ ከዚህ በፊት በG20 ጉባኤ ወቅት ባካሄድነው የሁለትዮሽ ስብስባችን ወቅት የተደረጉ ውይይቶችን ተግባራዊነት የተመለከተ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

‎በዋና ዋና ዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች፣ በቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እና የጋራ ፍላጎቶችን በውይይታችን ተመልክተናል ያሉ ሲሆን ይህም ፊንላንድ ኢትዮጵያ የምትረከበውን የኮፕ 32 ፕሬዝዳንትነት ድጋፍ ጨምሮ፣ የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን ዘርፎች ቀጣይነት ባለው ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት የተሰጠበት መሆኑንም አስፍረዋል።

በተጨማሪም ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስተር ጋር በውይይታቸው ወቅት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያለውን ትብብር ማሳደግ፣ በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት ላይ መምከራቸውን ጠቅሰዋል፡፡