EthiopiaInternationalNews

አመታዊ ገቢያቸው ከ50 ሺህ ብር በላይ የሆነ ዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ግብር እንዲከፍሉ የሚያስገድደው አዲስ ደንብ ስራ ላይ መዋሉ ተገለጸ፡፡

የዲጅታል አገልግሎት መድረክ አካውንት የተከፈተው ከኢትዮጵያ ውጭ መሆኑ ወይም ክፍያ የሚፈፀመው ከኢትዮጵያ ውጭ መሆኑ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነን የዲጅታል ይዘት ፈጣሪ የግብር ተጠያቂነት የሚያስቀር እንዳልሆነም በደንቡ ተጠቅሷል።

በደንቡ መሰረት ማንኛውም የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች በግብር ዓመቱ የሚያገኙት ጠቅላላ ገቢ ከ50 ሺህ ብር በላይ ከሆነ የገቢ ግብር የመክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ለዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ክፍያ የሚያመቻቹ ድረ ገጾች፣ የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ቦታዎች፣ የቀጥታ ስርጭት እና የማስታወቂያ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ ፈጣሪዎችን መረጃ ለታክስ ባለስልጣኑ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

የኦንላይን መድረኮቹ የክፍያ ጥያቄ የቀረበበትን አድራሻ፣ የሲምካርድ መረጃ እና የአይፒ አድራሻ መነሻ በማድረግ የፈጣሪዎችን ስም ዝርዝር፣ አድራሻ እና የተከፈላቸውን ገንዘብ መጠን በየሩብ ዓመቱ ለታክስ ባለስልጣኑ መላክ እንዳለባቸውም ደንቡ ያስቀምጣል።

የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የመያዝ እና ገቢያቸውን አሳውቀው በየሩብ ዓመቱ ግብር የመክፈል ግዴታ አለባቸው።

የታክስ ባለስልጣኑ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችን እንቅስቃሴ የመከታተል፣ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለባቸውን የመለየት እና ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የዲጂታል መድረኮች ጋር ተባብሮ የመስራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።