የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ የሚልኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና ከለጋሾች ድጋፍ በመብለጥ የአገሪቱ ትልቁ የውጭ ገንዘብ ምንጭ መሆኑን አስታወቀ።
ባንኩ ይሄን ያለው ኢትዮጵያን በተመለከተ ባወጣው ዝርዝር ሪፖርቱ ላይ ነው።
ባንኩ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2024 አመት 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ከሬሚታንስ ማግኘቷን ገልፆ የተገኘው ገቢ ከሃገራዊ ጥቅል ምርት ውስጥ ከ4-5 በመቶ የሸፈነ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ በዚሁ አመት ከሬሚታንስ ያገኘችው ገቢ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከተገኘው 4 ቢሊዮን ዶላር እና ከለጋሾች ከተገኘው የ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ በእጅጉ የሚበልጥ መሆኑን የባንኩ ሪፖርት ያሳያል።
ወደ አገሪቱ የሚላከው ገንዘብ በአብዛኛው ቤት፣ ጤና እና ትምህርት በመሳሰሉ ፍጆታዎች ላይ እንጂ በኢንቨስትመንት ላይ እንደማይውል የጠቀሰው ባንኩ የገንዘብ ፍሠቱን ለመጨመር የውጭ ምንዛሬን አስተማማኝነት መጠበቅ፣ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወጪዎችን መቀነስና የገንዘብ ቁጠባ ሥርዓቶችን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብሏል።
