የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከኃይል ሽያጭ እና ተጓዳኝ አገልግሎቶች 31 ቢሊዮን ብር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 114 በመቶ ማሳካቱን አስታወቀ።
የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ4 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ከጠቅላላው ገቢ 78 ነጥብ 98 በመቶው ከሀገር ውስጥ የተሰበሰበ እንደሆነ ገልጿል።
በተጨማሪም ተቋሙ በሩብ ዓመቱ 76 ነጥብ 62 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በማግኘት የዕቅዱን 126 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል በተቋሙ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ላይ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 78 ነጥብ 36 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ለግድቡ ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የአርሲሲ ኮንክሪት ሙሌት ውስጥ 82 ነጥብ 29 በመቶው መከናወኑን እና የስድስት ተርባይኖች የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎችም በዕቅዱ መሠረት እየሄዱ መሆኑን ተቋሙ አመልክቷል።
