ስምንት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላቀረቧቸው ተግዳሮቶች የፈጠራ መፍትሔን ማቅረብ የሚያስችል “ካማ” የተሰኘ የስታርታፖች መርሃግብር በይፋ ተጀምሯል፡፡
መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከኤ.ኤል.ኤክስ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ይህም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከኢትዮጵያውያን ኢንተርፕረነሮች፣ ስታርትአፖችና የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኝ “ካማ” የተሰኘ ስያሜ እንደተሰጠው ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ተጨባጭ ችግሮችን መፍታትና አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠር የሚችሉ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ እና ፈጠራ አቅም ያላቸው ወጣት ባለሙያዎች ቢኖራትም ሃሳባቸው ወደ ገበያ ቀርቦ ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት፣ ተቋማዊ ድጋፍና የገበያ ትስስር ለማግኘት ብዙውን ጊዜ እንደሚቸገሩ ተነግሯል፡፡
ይህን ተግዳሮት ለመፍታትም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከኤ.ኤል.ኤክስ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ካማ” የተሰኘ መርሃግብር ማዘጋጀቱን የተነገረ ሲሆን ይህም እነዚህን ሁለት አካላት በማገናኘት የሀገሪቱን የፈጠራ ሥነ-ምህዳር ለማሳደግ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ
በኢትዮጵያ የስታርታፕ ምህዳር ውስጥ እስካሁን ድረስ ብዙ ያለ መተሳሰር ክፍተት ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው መርሃ ግብሩ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተዘጋጀ መሆኑን እና ለዚሁ መርሃ ግብር 10 ሚሊየን ዶላር መመደቡን ተናግረዋል።
8ቱ የመንግሥት የልማት ድርጅት መፍትሔ የሚፈልጉ 21 የሚሆኑ ተጨባጭ የንግድና የአሠራር ችግሮችን በመለየት ማቅረባቸው የተነገረ ሲሆን ተቋማቱም የኢትዮጵያን አየር መንገድ፣ ቶፓን ሴኩሪቲ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትጵያ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ የፋይዳ ዲጂታል ሶሉሽን ኢንተርፕራዝና የኢትዮጵያ ቱሪስቶች ትሬዲንግ ኢንተርፕራይስ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የተመረጡ ስታርትአፕዎችና ባለሙያዎች ከተቋማቱ ባለሙያዎች ጋር በመሆን መፍትሔዎችን እንደሚነድፉና እንደሚያሻሽሉ የተነገረ ሲሆን ለመወዳደር ከተቀመጡ መስፈርቶች ውስጥ አገር በቀል ወይም ኢትዮጵያዊ ተቋም መሆን፣ የቀረቡ 21 ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችል ሀሳብ መያዝ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
ሌሎች ዝርዝር መስፈርቶችም እንደሚኖሩ የተጠቆመ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር እስከ 6 መቶ የሚሆኑ አመልካቾችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን ተነግሯል፡፡
ይህ “ካማ” የተሰኘው ሀገር በቀል መፍትሔዎችንና ስታርትአፕዎችን በማገዝና ወደ ገበያ የማሸጋገር ሂደትን ለማፋጠን ያለመው መርሐ-ግብር በአራት ዙሮች የሚተገበር ሲሆን፣ ሀሳቦችን ከመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅትና ሙከራ ጀምሮ ወደ አዋጭ የንግድ ዕድል፣ የገበያ ማስገባትና ማስፋት ያሸጋግራል ተብሏል።
መስፈርቱን የሚያሟሉ ስታርትአፕዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የልማት ድርጅቶቹ ያቀረቧቸውን የፈጠራ ፍላጎች በመመልከት በwww.kama.et አማካኝነት ማመልከቻቸውን በኦንላይን ማስገባት እንደሚችሉም የተጠቆመ ሲሆን ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችንም በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል።
የ”ካማ” የመጀመሪያ ዙር ማመልከቻ ከኅዳር 17 እስከ ታኅሣሥ 29 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል የተባለ ሲሆን በ1 ዓመት ጊዜ ውስጥ የፈጠራ ሃሳቦቹን ወደተግባር ለመለወጥ መታሰቡም ተገልጿል።
