የኢትዮጵያ እና የኬንያ ስምምነት
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ ጋር አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በ24 ብር ከ07 ሳንቲም ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።
የኃይል አቅርቦት ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እና የኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢ/ር ጆሴፍ ሲሮር ፈርመውታል።
በስምምነቱ መሰረት የኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ በአንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ለኢነርጂ 24 ብር 07 ሳንቲም እንዲሁም ለዲማንድ ቻርጅ 1 ሺህ 10 ብር ከ89 ሳንቲም የሚከፍል መሆኑን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኤሌክትሪክ ንግድ ለማጠናከር፣ በድንበር አካባቢዎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት እና የምስራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር ጌቱ ስምምነቱ የጋራ ህልም የሆነችውን ይበልጥ የተገናኘች ምስራቅ አፍሪካን እውን ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰው ኢነርጂ የሀብት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሕዝብ ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያደርስ ድልድይ ነው ብለዋል።
የኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢ/ር ጆሴፍ ሲሮር ስምምነቱ ከኃይል አቅርቦት ትስስር ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሰላምና የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
መረጃው ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘ ነው።
