EthiopiaNews

ከዛሬ ሐምሌ 13 ቀን እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት ገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ መካከለኛው፣ ሰሜን ምስራቅና ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ይኖራቸዋልም ነው ያለው  ።

በመሆኑም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ሰሜን የሀገራችን አካባቢዎች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አስታውቋል።

በተጨማሪም በመካከለኛዉ፣ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅና ደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸዉ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል፡፡

በተለይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከመካከለኛ እስከ ከባድ ወይም ከ11  እስከ 30 ሚሊ ሜትር  መጠን ያለው ዝናብ ሲያገኙ ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜንና በመካከለኛዉ የሀገሪቱ አካባቢዎችም በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር  በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል።