EthiopiaNews

ይህ የተገለጸው በኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር 46ኛው ዓመታዊ ሳይንሳዊ ጉባኤ ላይ ሲሆን፣ በጉባኤው የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች የማይገባ አጠቃቀም በአገሪቱ እየጨመረ መምጣቱ እና ይህም የሕክምና ስርዓቱን ውስብስብ እያደረገው መሆኑ ተነስቷል።

ጉባኤው “የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ ፈጠራን ማበረታታት እና የትብብር የሥራ ልምዶችን ማጠናከር” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በብዛት እየተስተዋለ ያለውን የመድኃኒት መቋቋምን ለመቀነስ የተቀናጀ ትብብር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትእዛዝ መውሰድ እና በባለሙያ የታዘዙ መድሃኒቶችን በትክክል አለመጠቀም የመድኃኒት የመፈወስ አቅምን በመቀነስ በሕዝብ ጤና ላይ ከባድ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ነው የተባለው፡፡

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶሌ ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትእዛዝ መውሰድ፣ የሕክምና መመሪያን ሳይከተሉ መጠቀም እና የታዘዘዉን መድሀኒት ሙሉ በሙሉ ወስደዉ ሳይጨርሱ ማቋረጥ የዚሁ ስጋት ምንጮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ዳንኤል አክለውም የጤና ባለሙያዎች ሕብረተሰቡ ስለ ትክክለኛ የመድኃኒት አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ በማስተማር እና በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ መድሃኒቶች አጠቃቀምን በመከታተል ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡በኬና ደሬሳ