EthiopiaNews

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው አዲስ ኃይል ማስቀጠያ ክፍያን በዱቤ ለሚከፍሉ ደንበኞች የሚጣለው የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን ተናገሩ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚ የወለድ ክፍያው መነሳቱ የአዲስ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስገባት ፍላጎት ያላቸው ሆነው የማስቀጠያ ክፍያውን በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ ዜጎች አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ኢንጅነር ጌቱ ገረመው አሰራሩ በተለይ የአዲስ ኃይል ማስቀጠያ ክፍያውን በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ ደንበኞች ክፍያውን በተወሰነ ጊዜ ተከፋፍለው እንዲከፍሉ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቀደም ሲል የዱቤ ክፍያ ጊዜው እስከ 24 ወራት እንደነበር እና ከ6 ወራት በላይ ለሚቆይ ክፍያ ከ3 እስከ 9 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይጣል እንደነበር አስታውሰው አሁን ይህ የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ተነስቷል ብለዋል።

ይህ አሰራር የዜጎችን የአንድ ጊዜ የክፍያ ጫና በማቃለል የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የአዲስ ደንበኞችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑንም ኢንጅነር ጌቱ ገረመው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት 1.1 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዟል።መረጃው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘ ነው።

#EBS
#EBSTVNEWS
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv