ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ የሚገኘው የወዳጅነት ፓርክ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ ገቢ ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድሎችንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ፈጥሯል ያሉት ፓርኩ ከዚህ ባለፈም ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ዜጎችና ጎብኝዎች የሚገናኙበት ሥፍራ መሆን መቻሉን አመልክተዋል።
የወዳጅነት ፓርክ ከኢኮኖሚያዊ እሴቱ ባሻገር ለጤና፣ ለአካል ብቃት፣ ለመዝናኛና ለሕብረተሰብ ትስስር ትልቅ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በጥሩ ሁኔታ የታቀዱ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የከተማነት ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚበረክቱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ፓርኩ በከተማዋ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች እየተገነቡ ላሉ ተመሳሳይ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ቀዳሚ ማሳያ ነው የተባለ ሲሆን እነዚህ አዳዲስ ቦታዎች እሴት የሚፈጥሩ፣ ዕድሎችን የሚያመቻቹ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ማዕከላት ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
