EthiopiaNews

በአዲስ አበባ በሚካሄደው 6ኛው ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ፣ ቴክኖሎጂና ኮስሞቲክስ ኤክስፖ ከ150 በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገለፀ።

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከህዳር 24 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ በሚገኘው አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር በሚካሄደው ኤክስፖው በርካታ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ነው ያስታወቀው።

በኤክስፖው የማምረቻ ዘርፍ፣ የምግብ ማቀነባበሪያ፣ የብረታብረት፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የፕላስቲክና ማሸጊያ ምርቶች እና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾች፣ ነጋዴዎችና አቅራቢዎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ኤክስፖው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን በማገናኘት የገበያ ዕድሎችን ለማስፋት፣ የኢትዮጵያን የማምረቻ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚመነጩ የንግድ ዕድሎችን ለመጠቀም ጠቃሚ መድረክ እንደሚሆን ነው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የገለጸው።በአቢስ ስዩም