ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ላይ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ቢያንስ 150 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልገው የሚደነግግ መመሪያን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አውጥቷል።
መመሪያው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ ክልል፣ በሐረሪ ክልል ወይም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ደግሞ ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን 120 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማቅረብ እንደሚያስፈልግም ይገልጻል።
ከሌሎቹ ክልሎች የውጭ አገር ዜጋ የቤት ባለቤት ለመሆን ዝቅተኛ ገንዘብ የሚጠየቀው በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልል ሲሆኑ የገንዘቡ መጠን ደግሞ 100 ሺህ ዶላር እንደሆነ ተደንግጓል።
በዚህ መመሪያ ላይ አንድ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ የቤት ባለቤት ለመሆን የማኅበረሰብ ሞራልና እሴት የመጠበቅ ግዴታ የተጣለበት ሲሆን በፍርድ ቤት ገደብ የሌለበት መሆን እንዳለበትም ሰፍሯል።
በመመሪያው መሠረት የውጭ አገር ዜጋ ማለት፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋን ሳይጨምር ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ወይም የሌላ አገር ዜግነት ያለው ማንኛውም ሰው እንደሆነም ተቀምጧል፡፡
