የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ 11 የሙያ ዘርፎች በመደበኛ ሥርዓተ ትምህርት ተካተው ሊሰጡ መሆኑን አስታወቀ።
ይህ የተባለው ከ2019 አ.ም ጀምሮ በመደበኛ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉት 11 የሙያ ዘርፎችን አስመልክቶ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ፣ የሥራና ክህሎት ቢሮ አመራሮች እና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች እንደተሳተፉ ተገልጿል።
በዚሁ መሠረት ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ብረታ ብረት ፣ቴክኖሎጂ፣ አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ አልባሳት ቴክኖሎጂ፣ ህንፃ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ ቧንቧ ሥራ፣ ሶፍትዌር ማበልጸግ፣ ሰብል አመራረት፣ ጤና ክብካቤ አገልግሎት፣ ሆቴል አገልግሎት፣ ፀጉር ሥራና ውበት አገልግሎት እና ምግብ ዝግጅት የመደበኛ የትምህርት መርሃግብር አካል ሆነው እንደሚሰጡ በመድረኩ ተነግሯል።
የሙያ ዘርፎቹን ለመተግበር የሚያስችል የመርሃ ትምህርት፣ የተማሪ ሞጁል እና የመምህር መመሪያ ዝግጅት በትምህርት ሚኒስቴር መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳድር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) አዲሱ አሰራር ተማሪዎችን በክህሎት በመቅረጽ አምራች ዜጋ ለማፍራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ቢሮ የዘርፍ ኃላፊ ዳግማዊት ግርማ በበኩላቸው ገበያው የሚፈልገው በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማቅረብ የተቀናጀ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።መረጃው የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ነው።
