የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማኅበር አንድ ኪሎ ግራም የኢትዮጵያ ቡና በ2,275 ዶላር መሸጡን ይፋ አደረገ።
በቻይና ሻንጋይ በተካሄደው የ”ሶለም ሶርሲንግ ሻንጋይ ኩዌይ” በተሰኘ ዓለም አቀፍ የቡና ጨረታ ላይ የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና በአንድ ኪሎግራም 2,275 የአሜሪካ ዶላር በመሸጥ አዲስ የዓለም ክበረ-ወሰን ማስመዝገቡን ማህበሩ ገልጿል።
ማህበሩ ቡናው በሲዳማ ክልል በንሳ አካባቢ በአርሶ አደሮች ተመርቶ በዘመናዊ የ”አናኤሮቢክ” ማቀናበሪያ ዘዴ የተዘጋጀ ልዩ ቡና እንደሆነ ገልፆ የቡናው ተፈጥሮአዊ ጣዕም፣ ልዩ መዓዛ እና ከፍተኛ የጥራት ደረጃ የዓለም አቀፍ ገዢዎችን ቀልብ መሳቡን አስታውቋል።
ማህበሩ ይህ የጨረታ ውጤት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለውን የበላይነት እና ተፈላጊነት በግልጽ ያሳየ ነው ብሏል።መረጃው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማኅበር የተገኘ ነው፡፡
